January 6, 2025

ለተሳካ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር አሁንም ቁልፍ ጉዳይ ነው እንላለን፡፡

img_5196

(ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌከ) የተሰጠ መግለጫ)

ከሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን) እና ከኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦሕኮ) ውህደት ሐምሌ 22/2004 የተመሠረተው ፓርቲያችን፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በአገራችን ውስጥ በተካሄዱት ምርጫዎች በአብዛኛዎቹ ስንሳተፍ ቆይተናል፡፡ ከውህደቱ በፊት በተካሄደው የ1997 ዓም 3ኛ ዙር ምርጫ ላይ ኦፌኮን የመሰረቱ ፓርቲዎች በተናጠል ተሳትፈው ብዛት ያላቸውን መቀመጫዎች ያሸነፍን ሲሆን፤ በተፈጸመው የኢህአዴግ የዘረፋ ተግባር ምክንያት ተመናምኖ ኦሕኮ 43 እና ኦፌዲን 11 መቀመጫዎችን በማግኘት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገብተዋል፡፡ በጬፌ ኦሮሚያም፤ ኦሕኮ 105 እና ኦፌዲን 10 መቀመጫዎች ነበሯቸው፡፡ ከዚያ በኋላ በነበሩት ምርጫዎች በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሕገ ወጥ ዘረፋ ምክንያት የሕዝባችንን ድምፅ ልንከላከል እንዳልቻልን ይታወቃል፡፡

እንዴዚያም ሆኖ ብዙዎች ተስፋ በቆረጡበት ጊዜ ቄሮ የሚባለውን የኦሮሞ ወጣቶችን በዋናነት ከአንቀሳቀሱት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ውስጥ ኦፌኮ አንዱ ሆኖ በቆራጥነት በመሳተፍ አባላቱን ውድ ዋጋ አስከፍሎ ላሁኑ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገም በአደባባይ ይታወቃል፡፡
ኦፌኮ በአንድ በኩል በ2012 ሊካሄድ በነበረው ምርጫም ሆነ በ2013 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ ያለመታከት ብሔራዊ መግባባት በሀገራችን እንዲፈጠር ስጠይቅ ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ለሀገራችን ሠላምና መረጋጋት፣ ለነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ከትንንሽ ስብሰባዎች እሰከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ ተናግረናል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ባወጣናቸው መግለጫዎችም አጥብቀን ጠይቀናል፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ለሥልጣን ባለው ስስት ምክንያት ምክራችንን አልተቀበለም፡፡ ብሔራዊ መግባባቱም ባለመሳካቱም እንደፈራነው አገሪቱም ሆነ እኛ አስቸጋሪ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል፡፡

Qeerroo and Qarree gathered at Meskel Square to welcome ABO

ላላፉት ወራትም ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ እንዲያስችለን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና የምርጫ ቦርድን ጨምሮ ለሚመለከታቸው ሁሉ ስናሳውቅ ቆይተናል፡፡

  1. በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ ጽ/ቤቶቻችን አንዳንዶች ተሰብረው ስለተዘረፉ፤ አንዳንዶች ደግሞ በአመራር አባላቱ ላይ ከደረሰ ዛቻና ማስፈራራት የተነሳ ስለተዘጉ እንዲከፈቱልን፣
  2. አባሎቻችን ከላይኛው እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ያሉትና የፓርቲያችንን ምርጫ ውድድር ሊያስተባብሩ፣ ሊወዳደሩና ሊታዘቡ የሚችሉ በተለይ በዞንና ወረዳ እርከኖች ላይ የሚገኙ መታሰራቸውን፣ ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው አከባቢያቸውን ለቅቀው መሰደዳቸውን፣ በዋና ጽ/ቤት ደረጃ ምርጫውን እንዲያስተባብሩ ከተመደቡት አምስት አባላት ውስጥ አራቱ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀነ ጣፋ፣ አቶ ጃዋር ሲራጅ ሞሃመድ እና አቶ ሀምዛ አዳነ መታሰራቸውን፤ ይህ እርምጃም ምርጫውን እንዳንወዳደር ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑን ለሚመለከታቸው አሳውቀናል፡፡
  3. ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ እና መንግስታዊ መዋቅሩ የተደባለቀ ስለሆነ የፖለቲካ ምህዳሩ በመጥበቡ በነፃነት ተንቀሳቀሰን የፓርቲያችንን ፖሊሲ እና የፖለቲካ ፕሮግራም ለሕዝብ ማድረስ ያለመቻላችንን፣
  4. በገለልተኝነት ምርጫውን ያስፈፅማሉ የተባሉት የምርጫ አስፈፃሚዎችም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የተሞሉና ቀሪዎች ደግሞ ሕግ የማውጣት ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቀውን የሕዝብ ተወካዮች ምርጫን የማስፈጸም ልምድና ቁመና ላይ እንዳልሆኑ እና በሁለቱም በኩል ፍትሓዊ ምርጫ ያስፈጽማሉ የሚል እምነት እንደሌለንም ለምርጫ ቦርድ ደጋግመን አሳውቀናል፡፡
  5. በኦፌኮ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቆም ዘንድ ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት፣ ለኢፌዲሪ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ለኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃበ ሕግ አቤቱታ ብናቀርብም አባ ካና ያለን አካል የለም፡፡ እዚህ ላይ የበለጠ የሚገርመው ደግሞ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የኦፌኮን መሀከለኛ እና የበታች አመራሮችን በማሰርና በማሳደድ የላይኛው አመራር አካል እንድንሳፈፍ እያደረጉ፣ ጅብ እንኳን ወደ ማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ የሚለውን ተረት ረስተው፤ ሲፈልጉ ድርጅታችን ምርጫውን ፈርቶ ሊወጣ ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ማን ሕወሓትን አምርሮ ሲታገል እንደነበረ እንደረሳ ሰው፤ ለሕወሓት ልዩ ፍቅር ብለው ከምርጫ ውድድሩ ሊወጡ ነው ይሉናል፡፡
  6. በጣም ጥቂት ከሚባሉ በስተቀር በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ሜዲያዎች፤ በተለይም ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብር የሚተዳደሩት ሜዲያዎች በገለልተኝነት እንዳይሰሩ በመደረጋቸው ያጋጠሙን ችግሮች ናቸው፡፡

ስለሆነም፤ ድርጅታችን የተቋቋመው እንደማንኛውም ፓርቲ ተወዳድሮ የመንግስት ሥልጣን መያዝ መሆኑ ታውቆ በኃይል የተዘጉ ጽ/ቤቶቻችን ተከፍተውና የታሰሩ አባሎቻችን ተፈትተው እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ የምርጫ መርሐ ግብሩ ተሻሽሎና የፖለቲካ ምህዳሩ ለሁሉም ዜጎች ተመቻችቶና ከሁሉም በላይ ደግሞ በተሳካ ብሔራዊ መግባባት የታጀበ የተሳካ ብሔራዊ ምርጫ እንድናካሄድ አጥብቀን እየጠየቅን፤ ኦፌኮ ለዜጎቿ ሁሉ የምትሆን ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በሚደረገው ሠላማዊ ትግል ጎን በፅናት የሚቆም መሆኑን ዳግም እያረጋገጠ፤ የኢትዮጵያ ሐቀኛ ዴሞክራሲያን ኃይሎች እና የተረጋጋች አገር እንዲትፈጠር የምትመኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተገቢውን ድጋፍ እንድትሰጡን በአክብሮት ጥሪ እናደርጋለን፡፡

መጪው ጊዜ የነፃነት ጊዜ ነው!

እናመሰግናለን!

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ፊንፊኔ፤ የካቲት 23/2013

About Post Author