January 4, 2025

በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በጥናት ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወሩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ተናገሩ

በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቀዛቀውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት  መንግስት በዘርፉ ለመተግበር ካቀዳቸው ተግባራት መካከል የመንግስት የልማት ድርጀቶቹን በከፊልና አሊያም ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታነት ማዛወር ቀዳሚው መሆኑ ይታወቃል።

Ethiopia Business

በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በጥናት ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወሩ በማድረግ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ማነቃቃት እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ተናገሩ። በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቀዛቀውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት  መንግስት በዘርፉ ለመተግበር ካቀዳቸው ተግባራት መካከል የመንግስት የልማት ድርጀቶቹን በከፊልና አሊያም ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታነት ማዛወር ቀዳሚው መሆኑ ይታወቃል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ  የምጣኔ ሀብት ምሁራን የልማት ድርጅቶቹ በከፊል አሊያም ሙሉ በሙሉ  ወደ ግል ይዞታነት መሸጋገራቸው የስራ እድል በመፍጠር ጤናማ የንግድ ውድድርን ከማሳለጥ ረገድ ከፈተኛ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮምን የመሰሉ ግዙፍ የመንግስት ተቋማትን በከፊል ወደ ግል ይዞታነት የማሸጋገሩ ተግባር በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሱ አበርክቶ ያለው መሆን ምሁራኑ ገልፀዋል። መንግስት ይህን ውሳኔ ማሳለፉም በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት መነቃቃት እንዲፈጠር የማደረግ አቅም እንዳለውም ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ኩባንያ ባለቤት እና በዘርፉ የማማከር ስራ ላየ የተሰማሩት አቶ ያሬድ ሃይለመስቀል ውሳኔዉ የውጭ ባለሃበቶችን ሳይቀር የሳበ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እይታ መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ በግል ሴክተሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሊያሳድር እንደሚችል ይገመታል፡፡ በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ንጉሴ ስሜ  መንግስት ግዙፍ ተቋማትን በከፊል ወደ ግል ይዞታነት ለማሸጋገር የጀመራቸዉ እንቅስቃሴዎች በግል ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተደቀኑ የብድር አገልግሎት ውስንነትን የመሰሉ ስጋቶችን ለመቀነስ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር የሚከወኑ ስራዎች ጥንቃቄ የተሞላባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ዶክተር ንጉሴ አንስተዋል። በተለይም የማህበራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ አስፈላጊው ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ነው የሚናገሩት፡፡ በቀጣይ በሀገሪቱ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ አሰራር ጤናማ የገበያ ውድድርን በመፍጠር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የመንግስት የልማተ ድርጅቶችን በከፊል እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታነት ለማሸጋገር የሚስችል አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች  ምክር ቤት የቀረበ ሲሆም፥ምክር ቤቱ ጉዳዩን ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደላከውም ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

About Post Author