በኦሮሚያ ክልል በህገ ወጥ ግንባታዎች ላይ በሚወሰደው እርምጃ የሚያጋጥሙ ግድፈቶችን የሚያጣራና እርምት የሚሰጥ ግብረሃይል ወደ ስራ ገባ
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የቢሮው ሀላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ህግን የማስከበርና ከተሞች በታለመላቸው ፕላን እና የእድገት መስመር መሰረት እንዲያድጉና የህዝቦች ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚሰራው ስራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል በህገወጥ ግንባታዎች ላይ በሚወሰድ እርምጃ ሂደት የሚያጋጥሙ ግድፈቶች ካሉ ለማጣራትና መፍትሄ ለመስጠት የተዋቀረ ግብረ ሃይል ወደ ስራ መግባቱን የክልሉ መንግስት ገለፀ።
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የቢሮው ሀላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ህግን የማስከበርና ከተሞች በታለመላቸው ፕላን እና የእድገት መስመር መሰረት እንዲያድጉና የህዝቦች ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚሰራው ስራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ህግ የማስከበሩ ስራ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ባይሆንም በማስከበሩ ሂደት የሚያጋጥሙ ግድፈቶች ካሉ እያጣራ እርምት የሚሰጥ ግብረ ሃይል በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ትዕዛዝ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን ነው ያመለከቱት።
የተዋቀረው ግብረ ሃይል አጣርቶ በሚያቀርበው ሪፖርት መሰረትም የእርምት እርምጃ እንደሚሰወድም ጠቅሰዋል። በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማም 12 ሺህ ቤቶች ህገወጥ መሆናቸው መለየቱን በመጥቀስ፥ በተደረገው ቅድመ ማጣራት ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቦታዎችና ይዞታዎች ከከተማዋ ማስተር ፕላን የማይጋጩ በመሆናቸው በህጋዊ ይዞታዎች ውስጥ እንዲካተቱ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም ባለፈው ዓመት 1 ሺህ ቤቶች ከማስተር ፕላኑ ጋር የሚጋጩ በመሆናቸው መፍረሳቸውንም አስታውቀዋል። ሰሞኑን ደግሞ ህጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው 347 ቤቶችና የተከለሉ ይዞታዎች መሆናቸውን አቶ አድማሱ ተናግረዋል። የሰሞኑ ህግን የማስከበር ስራ በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል የሚናፈሰውን ወሬ ለማጣራትም ትናንት የፌደራል እና የክልሉ የስራ ሀላፊዎችን የያዘ ቡድን በስፍራው ተገኝቶ ማጣራቱን እና እርምጃዎች ህገወጦች ላይ ብቻ ያነጣጠረ መሆኑን እንዳረጋገጠ ገልፀዋል።
ሀላፊው የክልሉ መንግስት የመሬት አስተዳደር አጠቃቀም በተገቢው መልኩ እንዲተገበር መስራቱን እንደሚቀጥልም በማስታወቅ፥ በክልሉ 25 ከተሞች ባለፈው አመት የተጀመረው የማስተካከል ስራ በዚህ አመትም ቀጥሎ እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል።