January 9, 2025

ኢሕአዴግ “ከጥቂት ወራት” በኋላ ከአጋሮቹ ይዋሐዳል

ኢሕአዴግ አጋሮቹን ጨምሮ ወደ አንድ ፓርቲነት ለመዋሐድ መዘጋጀቱን የግንባሩ ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ይኸን ያሉት በዛሬው ዕለት ከሐረሪ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር እና ከጋምቤላ ክልል ከተውጣጡ አጋር ድርጅቶችና የማኅበረሰብ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።

PM Abiy

ጠቅላይ ምኒስትሩ በመድረኩ አጋር ተብለው ከሚጠሩት አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ”እኛ ኢትዮጵያዊ ከሆንን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በሁሉም ጉዳይ ለመወሰን የገዢው ፓርቲ አካል መሆን እንፈልጋለን፤ ከእኛም ውስጥ ብቃት ያላቸው ሰዎች ካሉ ጠቅላይ ምኒስትር መሆን የሚችሉበት ዕድል ክፍት መሆን አለበት” የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸው እንደነበር ተናግረዋል።

 

ጠቅላይ ምኒስትሩ “ከጥቂት ወራት በኋላ ኢሶሕዴፓ የሚባል የለም፤ የአፋር ፓርቲ የሚባል የለም፤ የቤኒሻንጉል የሚባል ፓርቲ የለም፤ የኦሮሞ ፓርቲ፤ የአማራ ፓርቲ የሚባል የለም። ሁላችን ያለንበት አንድ የኢትዮጵያ ፓርቲ በመፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚነጋገርበት፤ እኩል የሚወስንበት፤ ድምጹ የሚሰማበት፤ ከየትኛውም ጫፍ ብቃት ያለው ሰው ለየትኛውም ኃላፊነት ክልከላ የማይደረግበት ሥርዓት ለመፍጠር ለውጡ በፍጥነት እየተጓዘ ይገኛል” ብለዋል።

 

ከውይይቱ በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተቀንጭቦ የተላለፈው ንግግራቸው ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲ ይሆናል የሚል አንድምታ ቢኖረውም አሁን ያለውን የግንባር አወቃቀር ቀይሮ ውሕድ ለመሆን ስለመዘጋጀቱ ግን የታወቀ ነገር የለም።

የኢሕአዴግ አጋር ተብለው የሚጠሩት አምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕዴን)፣ የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) እና የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) ናቸው።

አምስቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት ለመቀበል ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑን ያስታወቀው ኢሕአዴግ ባለፈው መጋቢት 2010 ዓ.ም. በሐዋሳ በተካሔደው ድርጅታዊ ጉባኤ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ቢጠበቅም አገሪቱ በገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ ሳይሳካ ቀርቷል። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን ላለፉት 28 ዓመታት በበላይነት የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ሲከተል የቆየው አሰራር አጋር የሚላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ያገለለ እንደሆነ ተንታኞች ይወቅሳሉ።

 

 

 

 

About Post Author