January 6, 2025

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት ምሳሌ የመሆን ብሩኅ ተስፋ አላት- ዊቲኒ ሽኔይድማን

በጠቅላይ ሚንስትሩ እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም ስራዎች በስኬት ከተጠናቀቁም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት መካከል ግንባር ቀደም ሆና ብቅ እንደምትል የማያጠራጥር ነው ሲሉ ጸሐፊው ገልጸዋል።

7C9C04FA-4217-4D4F-A0C7-393EBE852C0D

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት ምሳሌ የመሆን ተስፋ አላት ሲሉ ዊቲኒ ሽኔይድማን ገለጹ።

በግሎባል ኢኮኖሚና ልማት የአፍሪካ እድገት እንቅስቃሴ (Global Economy and Development, Africa Growth Initiative) አባል የሆኑት ዊቲኒ ሽኔይድማን አፍሪካ ኢን ፎከስ በተባለው ድረ ገጽ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ እየወሰደች ያለው ሪፎርም ረጅም ርቀት ያስጉዛታል።

የመንግስትን በኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት ምሳሌ አድርጎ ያወሳው ጽሑፉ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 15 ዓመታት 10 በመቶ  የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብም በአህጉሩ የተሻለ ዕድገት ካሚያመጡ አገራት ተርታ እንደሚያሰልፋትም ጠቅሰዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በኢኮኖሚው አለማሳተፉን እንደ ጉድለት የሚያነሱት ዊትኒ ሽንድማን፤ የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም  በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች ላይ መዋዕለ ነዋይን በስፋት  በማፍሰስ የሚታይ ለውጥ ማስመዝገቡን አወድሰዋል።

የ12 ወራት የስልጣን ቆይታ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ መሪነት ከመጡ በኋላ የፖለቲካውን ምህዳር የማስፋትና በኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞቹ የታዩ ለውጦች መኖራቸውን አስረድተዋል።

በጠቅላይ ሚንስትሩ እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም ስራዎች በስኬት ከተጠናቀቁም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት መካከል ግንባር ቀደም ሆና ብቅ እንደምትል የማያጠራጥር ነው ሲሉ ጸሐፊው ገልጸዋል።

በመንግስት ባለቤትነት የተያዙ አንዳንድ ተቋማትን ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር እቅድ መኖሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማድረግ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካካል በአዎንታዊ  የሚታይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም በማድረግ በኩል የጎላ ለውጥ አለመታየቱ የገለጹት ዊትኒ፤ ለአብነትም በመንግስት የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘርፉን ግማሽ ድርሻ ይዞ ደካማ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ለመንግስት የሪፎርም ጥረቶች ዕንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።

የፋይናንስ ሴክተሩ ውጤታማ እንዲሆን ሌሎች የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ባንኮች በአገሪቷ የባንከ ዘርፍ እንዲሰማሩ መፍቀድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም እንቅስቃሴዎች ስኬታማነት እርግጠኛ ለመሆን ጊዜው ገና መሆኑን ያወሱት ጸሐፊው፤ በአገሪቷ በርካታ እድሎች መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም።

ሆኖም በመንግስት እየተመራ ያለውን ኢኮኖሚ፤ ገበያ መር ወደ ሆነው ዕድገት ማሸጋገር እና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሪፎርም ማካሄድ የለውጡ እንቅስቃሴዎች መካከል ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑም ጠቅሰዋል። Author

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የቻይናን ቀልብ መሳብ ከቻሉት ቀዳሚዋ አገር ኢትዮጵያ አንዷ ናት ያሉት ጽሐፊው፤ የኢንደስትሪ ፓርኮችን በመገንባት  በቀላል የማምረቻው ዘርፍ በተለይም በጨርቃ ጨርቅና በአልባሳት ምርትና ወጪ ምርቶች ላይ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ባለሀብቶችን በመሳብ በኩልም  ግንባር ቀደም መሆኗን አትተዋል።

በአሁኑ ወቅት  ወደ 45 ሺህ የሚሆኑ የስራ እድሎችን ለኢትዮጵያውያን የፈጠሩ በመንግሰት የተገነቡ 5 የኢንደስትሪ ፓርኮች እና 4 በግል ባለሀብቶች የተገነቡ ፓርኮች መኖራቸውን በዋቢነት አውስተዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2025 ሰላሳ የኢንደስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ራዕይ ያላት መሆኗን ጠቅሰዋል።

በእነዚህም  ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰፊ የስራ እድል መፍጠርና በወጪ ምርቶች የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ እንዲሁም የአምራች ዘርፉ ለምጣኔ ሀብት ምርታማነት የሚያሳደርውን ተጽኖ ከ5 ከመቶ ወደ 22 በመቶ ለማሳደግ እቅድ መያዟንም ጠቁመው፤ በዚህም ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ድርጅቶችም  ከአገሪቷ ምርቶችን እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዶክተር አብይ ጥረቶች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ያወሱት ጸሐፊው፤ ለአብነትም የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የፈቀደው የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ የበጀት ድጋፍ ባንኩ ለአገሪቷ ብድር ከከለከለ ከ13 ዓመታት በኋላ ከሰሀራ በታች ባሉት የአፍሪካ አገራት ከተሰጠው ትልቁ ብድር መሆኑን ገልጸዋል።

የአቡ ዳቢ መንግስትም በ2 ቢሊዮን ዶላር ዘመናዊ የመሓል ከተማ ግንባታም በዋቢነት በማውሳት።

በመጀመሪያዎቹ የሥራ ቆይታቸውም  በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ነጻ ማድረጋቸው የሚያስወድሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የነበራቸውና ከ20 ዓመታት በላይ የቆየ የጠላትነት ግንኙነትም ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ማድረጉ ሌላ በአጭር ጊዜ ወስጥ ካሳኩትና ዓለምን ካስደመሙት አስገራሚ ለውጦች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጸሐፊው አስታውሰዋል።

በቅርቡ የሶማሊያን ፕሬዝዳንት ከኬንያው ፕሬዝዳንት ጋር እንዲገናኙና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እንዲያንሰራራ ጥረት ማድረጋቸውም  ከኢትዮጵያም አልፈው በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ግንኙነቱ ላይ ጉልህ ድርሻ እያሳደሩ መሆኑንም ዘገባው አትቷል።

በተጨማሪም አፍሪካውያን ተጓዦች በኢትዮጵያ ያለ ቪዛ  ጥያቄ እንዲዘዋወሩ መፈቀዱ እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ስምምነት በፓርላማ መጽደቁ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ በቅርቡ ከታዩ ለውጦች በዋነኛነት ተመልክቷል ሲል ጽሐፊው ተናግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ሰፊ ስራ እየሰሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ያንን ለውጥ በአገር ውስጥ የሰላምና መረጋጋት ማገዝ እንዳለባቸውም በጽሑፉ ተወስቷል።

የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆምና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግርን ለመፍታት የአገሪቱ ፓርላማ የእርቅ ኮሚሽን ማቋቋሙ ለዚህ አጋዥ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ መንግስት ቅድሚያ ከተሰጣቸው አገራት መሆኗን ያወሳው ጽሑፉ፤ ዶክተር አብይም ከአሜሪካው  ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጋር መወያየታቸውና ፕሬዝዳንቱም የዶክተር አብይን ታሪካዊ የሪፎርም ስራዎችን ማድነቃቸው እንደ ስኬት አንስቷል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚጠበቁ ቁልፍ ተግባራት መካከልም እ.አ.አ በ2020 ለሚካሄደው ምርጫ ዝግጅት ማድረግ ሲሆን የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የነበሩትን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ  የአገሪቷ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር እንዲሆኑ መሾማቸው ደግሞ ለዚህ መልካም ጅማሬ መሆኑን ዊቲኒ ሽኔይድማን አንስተዋል።

 

 

About Post Author