January 6, 2025

የሞፈር፣ የሰይፍና የመጽሓፍ አገር?

አንድ በጣም የማከብረው ምሁር፣ ‘ኢትዮጵያ የሞፈር፣ የሰይፍና፣ የመጽሐፍ አገር ነው፣” ይል ነበር። ይህም ማለት፣ አገሩ፣ የእርሻ/የግብርና፣ የጦር/የነፍጥ፣ እና የክህነት/የተፃፈ እውቀት አገር ነው እንደማለት ነው።የዚህ አንድምታ ደግሞ፣ የአገሩ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ (political economy)፣ በአርሶ አደሩ/በገበሬው፣ በወታደሩ/በሽፍታው፣ እና በካህናቱ/ጽሁፍ አዋቂ ሊቃውንት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ይመሠረታል ማለት ነው።

Dr Tsegaye

አንድ በጣም የማከብረው ምሁር፣ ‘ኢትዮጵያ የሞፈር፣ የሰይፍና፣ የመጽሐፍ አገር ነው፣” ይል ነበር። ይህም ማለት፣ አገሩ፣ የእርሻ/የግብርና፣ የጦር/የነፍጥ፣ እና የክህነት/የተፃፈ እውቀት አገር ነው እንደማለት ነው።

የዚህ አንድምታ ደግሞ፣ የአገሩ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ (political economy)፣ በአርሶ አደሩ/በገበሬው፣ በወታደሩ/በሽፍታው፣ እና በካህናቱ/ጽሁፍ አዋቂ ሊቃውንት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ይመሠረታል ማለት ነው።

“የኢትዮጵያ ዘመናዊነት”፣ በነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን ግንኙነት የተስተካከለ (እናም ፍትሓዊ) ያደርጋል የሚል ተስፋ ነበረ። ለዘመናት የበላይነት የነበራቸው ሰይፍ የጨበጠው ክፍል (ወታደር/ሽፍታ) እና መጽሓፍ ያነገበው (ካህን/’አዋቂ’) ነበሩ። ሁለቱ ክፍሎች አንጋሽ/ነጋሽ እና ቀዳሽ/አወዳሽ በመሆን በአርሶ አደሩ/በገበሬው ላይ የበላይነት ኖሮአቸው መቆየታቸው ይታወቃል።

የ’አዋቂዎቹ’ ክፍል የቤተእምነት መጻሕፍትን አስቀምጦ ወይም ትቶ፣ ሁሉን አቀፍ የሆኑ ጠቅላላ መጻሕፍት (secular scripts) ወደ ማንበብ ሲሸጋገር እና የራሱን የንቃት ዘመን (enlightenment) ሲጀምር፣ ‘የተማሪዎች ንቅናቄ’ ተብሎ ይሄን የከራረመ የብረትና የክታብ የበላይነት ለመሻር ተንቀሳቀሰ። የአርሶአደሩን የመሬት ባለቤትነት አረጋግጦ የተስተካከለና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ግንኙነት ከማማጣቱ በፊት ሰይፍን በታጠቁ ኃይሎች ተቀደመ። በምላሹም፣ ይሄም ክፍል እንደ ባላንጣው የወታደር ክፍል፣ ሰይፍ በመያዝ በሽፍትነት ‘ተከራከረ’። ሲያሸንፍም በሰይፍ ሥልጣኑን አጸና። ሰይፍና መጽሓፍን ቀላቅሎ (ወይም እያጣቀሰ) ያንን ምስኪን ባለሞፈር፣ የተለያየ ‘የልማት ፕሮግራሞች’ እየቀረፀለት፣ አንዴ ወዲህ፣ አንዴ ወዲያ እየገፋው በበላይነት ለማስተዳደር ሞክሮ ሞክሮ፣ የአርሶ አደሩ ልጆች በሆኑ ወጣቶች (ቄሮዎች) ግፊት ከስልጣን ማዕከል ወደ ጠርዝ ተገፋ።

አሁን ጥያቄው፣ “የኢትዮጵያ ‘ዘመናዊነት’፣ አርሶ አደሩ በዴሞክራሲያዊ አግባብ መሬቱን፣ ምርቱን እና አገሩን እንዲያስተዳድር ያደርጋል ወይ?” የሚለው ነው? ይኼ የማሕበረሰብ ክፍል፣ እራሱን በፈቃዱ ከሞፈር አላቆ፣ ሌላ ዓይነት የምርት ግንኙነት ውስጥ ይገባ ይሆን? ‘አዋቂው’ ክፍልስ እውነት በ(ሕግ) መጽሓፍ መተዳደርና ማስተዳደርን ይለምድ ይሆን? ሰይፍስ ከፖለቲካው ምህዳር ወደ ሰገባው፣ ወታደሩም ከሥልጣን አደባባይ ወደ ምሽጉ፣ ይመለስ ይሆን? ፖለቲካችንስ ከብረት፣ ውትድርናስ (ከካድሬያዊ) ፖለቲካ ይላቀቅ ይሆን? ሰሞኑን… ከበረታን፣ በነዚህ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ ነገር እንላለን።

ይጠብቁን።

 

 

About Post Author