የአቶ በቀለ ገርባ የእምነት ክህደት ቃል!
በመጀመሪያ ደረጃ ብሔርን ከብሔር አጋጭተሀል የሚል ውንጀላ ቀርቦብኛል። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ብሔሮች በእኩልነትና በሰላም እንዲኖሩ በጋራ ስላደረግነው ጥረት አንደኛ ተከሳሽ አቶ ጀዋር መሀመድ ያነሳውን ሳልደግም አስተዳደጌ፣ የፖለቲካ አቋሜ፣ እምነቴና ድርጊቴ ይህንን የማያመላክት መሆኑን ባጭሩ ገልጬ ማለፍ ብቻ እፈልጋለሁ።
በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች የወንጀል ችሎት ‘ፍትሕ አዳራሽ’ ውስጥ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም
ክቡር ፍርድ ቤት፣ ለተከሰስኩበት ወንጀል በአጭሩ ፈጽሜያለሁ ወይንም አልፈጸምኩም ብዬ መልስ ብሰጥ ደስ ባለኝ ነበር። ነገር ግን ክሱ ያደረግኩትንም ያላደረግኩትንም፣ ያልኩትንም ያላልኩትንም፣ የፖለቲካ አቋሜ ነጸብራቅ የሆነውንም ያልሆነውንም ደራርቶ ያቀረበ በመሆኑ ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ሀሳቤን መስጠት ግድ ሊሆንብኝ ነው።
በክሱ ውስጥ የተመላከቱት ውንጀላዎች ሊያስከስሱኝ የማይችሉ በአብዛኛው የፖለቲካ አቋሞቼ ሲሆኑ እነሱም፦
- የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ብሔር ብሔረሰቦችን ለማጋጨት
- ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ
- መንግስት የስልጣን ዘመኑ መስከረም 30 ያበቃል በማለት
- የኦሮሞን ህዝብ ሲገድልና ሲጨርስ የነበረው ነፍጠኛ ነው። በነፍጠኛ ስርአት ስር መተዳደር የለብንም በማለት ስትቀሰቅስ ቆይተህ የአርቲስት ሀጫሉን ሞት ምክንያት በማድረግ ለብዙ ሰዎች ሞትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆነሀል የሚሉት ናቸው።
በመጀመሪያ ደረጃ ብሔርን ከብሔር አጋጭተሀል የሚል ውንጀላ ቀርቦብኛል። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ብሔሮች በእኩልነትና በሰላም እንዲኖሩ በጋራ ስላደረግነው ጥረት አንደኛ ተከሳሽ አቶ ጀዋር መሀመድ ያነሳውን ሳልደግም አስተዳደጌ፣ የፖለቲካ አቋሜ፣ እምነቴና ድርጊቴ ይህንን የማያመላክት መሆኑን ባጭሩ ገልጬ ማለፍ ብቻ እፈልጋለሁ። የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በክርስትና እምነት ከተዛመድናቸውና እቤታችን ተቀምጠው ይማሩ ከነበሩ የጉሙዝ ብሔረሰብ አቻዎቼ ጋር ነበር። በኦሮሞና በጉሙዝ አጎራባች ህዝብ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ በነበረበት ጊዜ ከአንደኛ ተከሳሽ ጋር ሆነን ችግሩን ለመፍታት ወደ ስፍራው እንድንጓዝ ካስገደዱኝ ምክንያቶች አንዱ ያ የነበረን የልጅነት ፍቅር ነበር። በእምነቴ የሰው ልጅ እኩልና ነጻ ሆኖ የተፈጠረ መሆኑን ስለማምን በተገኘሁበት ማህበረሰብ ውስጥ ቶሎ የመላመድ፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን የመማር ተተሰጥዖ አለኝ። አንዳንዶች ባንድ ስፍራ ሰላሳና አርባ ዓመት ኖረው የሚኖሩበትን ህብረተሰብ ቋንቋ በማይናገሩበት ሀገር፣ ከብዙ አመታት በፊት ጤና ረዳት ሆኜ ጌዴኦ ዞን ውስጥ ገርቦታ የሚባል ክሊኒክ ስመደብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለህዝቡ ካለኝ ክብር የተነሳ ቋንቋውን ለምጄ ያለ አስተርጓሚ ህመምተኞችን ማከም ችያለሁ። ብዙ ያገራችን ብሔሮች በዓላቸውን ሲያከብሩ ወሳኝ ፖለቲካዊ ስብሰባዎችን ሲያካሂዱ ተጋብዤ ታድሜያለሁ። በፖለቲካ አስተሳሰቤ በዴሞክራሲና በውይይት የማምን፣ በትግል ስልት የነማህተመ ጋንዲ ሳትያግራሀና የማርቲን ሉተር ኪንግ የሰላማዊ ትግል ተከታይ ነኝ። የሰው ልጅ መመዘን ያለበት በቆዳ ቀለሙ ሳይሆን በባህሪው መሆን እንዳለበት “ህልም አለኝ” በሚለው ዝነኛ ንግግሩ አስረግጦ የተናገረውን ታዋቂ የሲቪል መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ መጽሀፍ ወደ አማርኛና አፋን ኦሮሞ በመተርጎም እኛም ሰውን የምንለካው በብሔሩ ሳይሆን በግል ባህሪው መሆን እንዳለበት ትምህርት እንድንቀስምበት ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ባጠቃላይ ወደ ፖለቲካው ከመግባቴ በፊትም ሆነ ከገባው በኋላ አንድም ቀን በንግግርም ይሁን በጽሑፍ የየትኛውንም ብሔር ክብር ዝቅ የሚያደርግ ወይም የሚያንቋሽሽ ተግባር ፈፅሜ አላውቅም። ይህንን ማንም ሊያረጋግጥብኝ አይችልም። ነገር ግን እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በሀሰት ስሙ እንደኔ የጎደፈ የጥላቻ ዘመቻ የተደረገበት መኖሩን እኔ አላውቅም።
2ኛው ውንጀላ ህዝብን በመንግስት ላይ አነሳስተሀል የሚል ሲሆን በአገራችን በየጊዜው ከተፈራረቁ መንግስታት ባህሪ የተነሳ መልካም ግንኙነት እንዳልነበረኝ አልክድም። ከወታደራዊው መንግስት ሳንግባባ ዘመኑ አለቀ፤ ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ አመት ሳይሞላው አሰረኝ፤ በዚህ ከፍተኛ ፌዴራል ፍርድ ቤትም ይኸው ለሶስተኛ ጊዜ ቀርቤያለሁ። በ2002 ዓ.ም የምርጫ ዘመቻ ወቅት የመሬት ወረራና የገበሬዎች መፈናቀልን በማስመልከት ከረር ያለ ትችት በማቅረቤ ጥርስ ተነክሶብኝ እዚሁ ከተማ ውስጥ በሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያስተማርኩ በ2003 ዓ.ም ከክፍል ጠርተው አስረውኝ ሶሎሎ ሄደህ የኦነግ ወታደራዊ ስልጠና ወስደሀል ተብዬ ተከስሼ አቃቢ ህግ ባሰለጠናቸው የሀሰት ምስክሮች ተመስክሮብኝ አራት አመት ታስሬ ወጥቻለሁ። ያኔ ያደረግኩት ማለትም በወቅቱ የነበረውን ግፍ መናገሬ ህዝብን በመንግስት ላይ ማነሳሳት ሆኖ ከተቆጠረ አዎ አድርጌያለሁ።
እንደገና በ2008 ዓ.ም የመሬት ዘረፋው፣ ግፉ፣ አፈናው፣ አድሎውና ኢ-ዴሞክራሲያዊነቱ አይን አውጥቶ ህዝቡን ባስጨነቀበት ወቅት ድርጊቱን በመቃወሜ በአሸባሪነት ተከስሼ ዳግም እስር ቤት ገባሁ። በወቅቱ በርግጥም በሰላማዊ ትግል ህዝቡን ለማነሳሳት ሞክሬያለሁ። በስልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ የህዝቡን የተቃውሞ ማዕበል መቋቋም ባለመቻሉ በውስጡ የነበሩ የለውጥ ሀይሎች በሚዲያዎች ላይ ብቅ እያሉ የህዝቡን ሀሳብ በመደገፍ “አሸባሪዎች እኛ ነን፣ ህዝቡ ስህተት የለበትም፣ በደል አድርሰናል፣ ሰርቀናል” ብለው መናገር በመጀመራቸው ይህንኑ ፍርድ ቤት መጥተው እንዲመሰክሩልን የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖችን በመከላከያ ምስክርነት ጠርተን በቀጠሮ ላይ እንዳለን ፓርቲው በውስጡ ባደረገው ሽግሽግ በወቅቱ ከፍተኛ ነው የተባለ ለውጥ ተደርጎ የእኛም ክስ ተቋርጦ ከእስር ቤት ወጣን። ለውጡ ሲደረግ መላው ህዝብ ትልቅ ተስፋ ያደረገበት ሲሆን እኔም ፈጣሪን ካመሰገኑት ውስጥ አንዱ ነበርኩ። እግዚአብሄር ጸሎታችንን ሰምቶ መልካም ሰዎችን የሰጠን አድርጌ ወሰድኩ። የጠቅላይ ሚኒስትሩና የሌሎችንም ልብ የሚነካ ንግግር ስሰማ በእጅጉ ተማረኩ። ከዚህ የተነሳ ወደ ውጪ አገር ተጋብዤ ስሄድ በተገኘሁባቸው መድረኮች ሁሉ ይህን መንግስት እንዲደግፉ ተማጸንኩ። ከዋሺንግተን እስከ ኒውዮርክ፣ ከአትላንቲክ ካውንስል እስከ ስቴት ዲፓርትመንት ተመላልሼ የለውጥ ቡድኑ ፋታ አግኝቶ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን አጠናክሮ የተሳካ ምርጫ ለማካሄድ እንዲችል ድጋፍ ይደረግለት በማለት ተከራከርኩ። በአንድ ወቅት በዚህ ቡድን ላይ ከነበረኝ እምነት የተነሳ እንዲህ አይነት መልካም መሪዎች ካገኘንማ ካሁን በኃላ ለኔ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ መቆየት አስፈላጊ ላይሆን ስለሚችል በመደበኛ ስራዬ ላይ ብቻ ለመወሰን እስከማሰብ ደርሼ ነበር። የዋህነት ነበር።
በአጠቃላይ ለውጡ እንዲህ በፍጥነት ሀዲዱን ይስታል ብዬ አልገመትኩም ነበር። ሺዎች በወጡበት እስር ቤት አስር ሺዎች ይገባሉ ብዬ አላሰብኩም። አንድ ማዕከላዊ ተዘግቶ ት/ቤቶች ሁሉ ማዕከላዊ እስር ቤት ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም። ባዶ እጃቸውን ታንክ ፊት ቆመው የታገሉ ወጣቶች ‘ሸኔ’ ተብለው ተገድለው፣ ይህን ያህል ደመሰስን ተብሎ እንደ ጀብድ በሚዲያ ይታወጃል ብዬ አልገመትኩም። የኦሮሞ እናት ዳግም ታለቅሳለች ብዬ ፈፅሞ አላሰብኩም። እዚሁ አገር ውስጥ ለዘመናት የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆኖ የኖረ ምሁር እያለ ዲያስፖራው እየበረረ መጥቶ መሬት እየተቀራመተ ስለ ትግል ያስተምረዋል ብዬ ከቶ አላሰብኩም ነበር። የገበሬ ቤት እያቃጠለ ከቦ የሚጨፍር የመንግስት ታጣቂ ይኖራል ብዬ እንዴት ልገምት እችል ነበር?
ገዢው ፓርቲ ለሁለት ተገምሶ ወታደሩ እርስ በራሱ ተዋግቶ መከላከያችን ተዳክሞ በሮቻችን ለባዕዳን እንዲህ ወለል ብለው ይከፈታሉ ብዬ እንዴት እገምታለሁ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች ‘ተፎካካሪ ናችሁ’ ተብለን ቢያንስ በስያሜው ተደስተን ሳንጨርስ ጽፈት ቤቶቻችን በሙሉ ተዘግተው፣ አባሎቻችን በሙሉ ታስረው፣ ከምርጫ እንወገዳለን ብለን ፈጽሞ አላሰብንም። ዘጠና ከመቶ በላይ የመንግስትና የመንግስት ደጋፊና ተደጋፊ የግል ሚዲያዎች በአንድ የብሔር ቁጥጥር ስር ሆነው በሌሎች ላይ ይዘምታሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር። ጭካኔንና ሬሳ መቁጠርን ባልተለመደ ሆኔታ እንለማመዳለን ብዬም አላሰብኩም። በአጠቃላይ እውነትና ውሸት በዚህ ፍጥነት ቦታቸው ተቀያይሮ ሁሉ ነገር (ሥልጣን፣ ሀብት፣ እውቀት፣ እምነትና ተቋም) ክብር ሲያጣ ዝም ብዬ ማየት ባለመቻሌ የማሰማው ተቃውሞ መንግስት ላይ ህዝብ እንደማነሳሳት ተቆጥሮብኝ ሊሆን ይችላል። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅተን፣ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተን የምንንቀሳቀሰው እንዲህ አይነቶቹን እኩይ የመንግስት ተግባራት በመጠቆም፣ ለህዝብ በማሳወቅ፣ በይፋ በማጋለጥና በመተቸት እንዲታረሙ በሰላማዊ መንገድ ጫና ለመፍጠር ነው። እንደ አንድ ዜጋና አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እነዚህ ተግባራት መብቴ ብቻ ሳይሆኑ ግዴታዎቼም ናቸው።
በ3ኛ ደረጃ የቀረበብኝ ውንጀላ “የገዢው ፓርቲ መንግስት የስልጣን ዘመኑ መስከረም 30 ያበቃል” በማለት ቀስቅሰሀል የሚል ነው። አገራችን ህገ መንግስት ያላት አገር ነች። ህገ መንግስቱ የቃልኪዳን ሰነዳችን ነው። ማንም እንደፈለገ የሚጥሰው አይደለም። የተጻፈውም በዋነኝነት ለአምባገነን መሪዎች ልጓም እንዲሆን ታስቦ ነው፤ ህገ መንግሥቱ መንግስታት በስልጣን ላይ ሊቆዩ የሚችሉት ለአምስት አመት ብቻ መሆኑን ምንም ክፍተትና ትርጉም በማያስፈልገው መልኩ ደንግጓል። ነገር ግን ገዢው ፓርቲ ስልጣኑን ለመልቀቅ ባለመፈለጉ ከራሱ ፓርቲ ብቻ የተውጣጡ በቀጥታ በህዝቡ ያልተመረጡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን ሰብስቦ ትርጉም በማያስፈልገው ህገ-መንግስታዊ ጉዳይ ላይ ትርጉም እንዲሰጡ በማድረግ በህገ ወጥ መንገድ የስልጣን ጊዜውን አራዝሟል።
ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የመንግስት የስልጣን ዘመን የሚያበቃው መስከረም የመጨረሻው ሳምንት (30) መሆኑንና ከዚያ በኃላ ስለሚኖረው መንግስት ሌሎች ፓርቲዎችም ሊመክሩበት እንደሚገባ በወቅቱ የአብዛኞዎቹ አቋም ነበር። ዛሬም ቢሆን አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ስልጣኑን ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ በህገ ወጥነት ይዞ የቀጠለ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይሄ ሊያስከስሰኝ አይችልም። ይልቅ መክሰስ ያለብኝና መካስ የነበረብኝ እኔ ነበርኩ።
በ4ኛ ደረጃ “የኦሮሞን ህዝብ ሲገድል የነበረው ነፍጠኛ ነው፣ በነፍጠኛ ስርአት ስር መተዳደር የለብንም” ብለሃል የሚል ውንጀላም አለ። የነፍጠኛው ሥርዓት ይህን አላደረገም የሚል ካለ ይህ ያለንበት ስፍራ ፍርድ ቤት አይደለም ሊል ስለሚችል ለመግባባት እንቸገራለን። የነፍጠኛው ስርአት ስለፈጸማቸው ግድያዎችና በደሎች ብዙ የተባለለትና የተጻፈ በመሆኑ የእውቅ ታሪክ ጸሀፍትን ማለትም የእነ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ መሀመድ ሀሰንና ላጲሶ ጌዴሌቦን ስራዎች መመልከት በቂ ይሆናል። በክሱ ውስጥ ነፍ_ጠኛና አማራን ሆን ብሎ በማምታታት በመቅረቡ የሁለቱን ልዩነት ማየት መልካም ነው።
ነፍጠኛ ማለት ነፍጥ ይዞ የአንድን አካባቢ ህዝብ ወርሮ፣ የገደለውን ገድሎ የቀረውን አስገብሮ፣ መሬቱን በጉልበት ቀምቶ፣ ቋንቋውን ባህሉንና እምነቱን ያለ ፍላጎቱ ጭኖበት የሚገዛው ገዢ መደብ ነው። ይህ የነፍጠኛው ሥርዓት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተግባር የዋለው በኦሮሚያና በደቡቡ የአገራችን ክፍል ነው። የነፍጠኛን ሥርዓት ብዙዎቻችሁ በታሪክ ብቻ ታውቁት ይሆናል፣ ከመጽሀፍ አንብባችሁ ወይም ከሰው ሰምታችሁ ይሆናል። እኔ ግን በተግባር አውቀዋለሁ፤ ኖሬዋለሁ። የሰው ልጅ የዘር ማንዘሮቹ በኖሩበት ቀዬ መሬቱን ተቀምቶ፣ ተዋርዶ፣ ከሰው በታች ሆኖ አርሶ እራሱ ግን ጦሙን እያደረ ነፍጥ ይዞ የመጣን ጉልበተኛ ሲያበላ አይቻለው። አያቶቻችን ከብት ሲያሰማሩበት የነበረውን መሬት ከየት እንደመጣ በማይታወቅ ነፍጠኛ ተቀምቶ አባቴና ሌሎችም ከብቶቻቸውን ሽጠው መልሰው የገዛ መመረታቸውን ሲገዙ በልጅነቴ ከአባቴ ጋር ‘ነጭ ሽልንግ’ በአህያ ጭነን ሄደን ለነፍጠኛው ስናስረክብ አውቃለሁ። ታዲያ ይህንን ስርአት ያልታገሉ ምንን ይታገላሉ? ይህን በመሰለ ክፉ ሥርዓት ስር ለመተዳደር ፈቃደኛ አለመሆን ምን ያስከስሳል? እኔ አሁንም በእንዲህ አይነት ሥርዓት ስር መተዳደር አልፈቅድም።
እላይ እንደጠቀስኩት ነፍ_ጠኛና አማራ የተለያዩ ናቸው። ለአብነትም፦
- በተወለድኩበት፣ ባደኩበትና አሁንም ቤተሰቦቼ በሚኖሩበት አካባቢ በየዓመቱ ብዙ የአማራ ገበሬዎች ለስራ ፍለጋ ይመጣሉ። እንደ ማንኛውም ሰው ሰርተው፣ የድካማቸውን አግኝተው ብዙዎቹ ወደ መጡበት ይመለሳሉ። ጥቂቶች ይከርማሉ፤ አንዳንዶቹ እዚያው ቀርተው ያገባሉ፣ ይወልዳሉ። እነዚህ መሬት በጉልበት ለመቀማት የመጡ አይደሉም፤ አልተዋጉም፤ ማንነታቸውን በአገሬው ህዝብ ላይ አልጫኑም፤ ስለዚህ እነዚህ አማራ እንጂ ነፍ_ጠኛ አይደሉም።
- የከፍተኛ ትምህርቴን የተከታተልኩት በአማራ ክልል በቀድሞው ባህር ዳር መምህራን ኮሌጅ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ጓደኞቼ የአማራ ተወላጆች ናቸው። በስራ ላይ ስሰማራም የስራ ባልደረቦቼ አማራዎች ነበሩ። ነፍጥ የያዙ አይደሉም፤ ሰውም ያፈናቀሉ አይደሉም፤ እንግዛችሁ ብለውን አያውቁም፤ ማንነታቸውን በሌላ ላይ ለመጫን የሚሹ አልነበሩም፤ እነዚህ ነፍጠኞች አይደሉም። ስራ ላይ ከተሰማራሁ በኃላ በርካታ ጊዜያት የአማራን ገጠርና ከተሞች ጎብኝቻለሁ። የህዝቡን አኗኗር በሚገባ ተመልክቻለሁ። አኗኗራቸው ከተወለድኩበት አካባቢ ገበሬ አኗኗር ምንም ልዩነት የለውም። ይህን ህዝብ ነፍጠኛ ነው ማለት የፖለቲካ ድንቁርና ብቻ ሳይሆን ሃጢያትም ጭምር ነው።
- በንግድ ስራ የሚተዳደሩ የዚህ ብሄር ተወላጅ ወዳጆችም አሉኝ። ንግዳቸውን የሚያከናውኑበት ስፍራ ወይ በድካማቸው የሰሩት ነው አልያም ተከራይተውት ነው። ማንንም አልቀሙም፤ ማንነታቸውን በሌላ ላይ አልጫኑም። እነዚህ ዓማራ እንጂ ነፍ_ጠኛ አይደሉም።
ነፍጠኝነት ከመሬት ስሪት ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደ ሥርዓት የካቲት 1967 በታወጀው የገጠር መሬት አዋጅ ሥር መሰረቱ ተነቅሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስልተምርቱ (mode of production) የተለወጠ መሆኑ ቢታወቅም በአስተሳሰብ ደረጃ አቆጥቁጦ በኢትዮጵያ አንድነት ሽፋን የራሳቸውን ማንነት ብቻ የአገሪቱ ነጸብራቅና ወካይ በማድረግ የሌላውን ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና ታሪክ በአጠቃላይ ብዝሀነትን አናንቆ እንደ ዘረኝነት በመቁጠር ህዝቦችን ማሸማቀቅ እየጎላ መጥቷል። ይባስ ብሎ ዓለም እንደ ጸያፍና አሳፋሪ ታሪክ በመቁጠር ህዝቦችን ይቅርታ የጠየቀበትን ሥርዓት አምሳያ ከተቀበረበት ጉድጓድ አውጥቶ እንደ አኩሪ ታሪክ በመቁጠር “የነፍጠኛ ልጅ ነኝ” የሚል ቲሸርት በመልበስ መንጎማለል ተጀምሯል።
ዘመናዊው የነፍ_ጠኝነት አስተሳሰብ የሚቀነቀነው በበርካታ ዘርፎች ሲሆን ዘመቻው የሚካሄደው በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ባሉ የዚህ አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ ሰዎች፣ በመንግስትና በግል ሚዲያዎች፣ በአክቲቪስቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ነን በሚሉ ግለሰቦች፣ በሲቪክ ማህበራት፣ በገጣሚያንና በደራሲያን፣ በምሁራንና በተመራማሪዎች፣ በኮሜዲያኖች እና በስፖርት ደጋፊዎች ስም በአገር አንድነት ጭምብል ነው።
ዛሬ የአገሪቱ ፖለቲካ በሁለት ጎራዎች የተከፈለ ነው። አንደኛው አሁን የጠቀስኳቸውን ተቋሞችን በመጠቀም የምንከተለውን ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም በማፍረስ፤ ህገ-መንግስቱን በመለወጥ የቀድሞውን ሥርዓት (የአንድን ወገን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ) የበላይነት ለማስፈን የሚፈልግና በሌላ በኩል ብዝሀነትን የሚያስተናግድና የሚያከብር ስርአት በሂደት እየጎለበተ እንዲሄድ የሚፈልግ ጎራ አለ። የመጀመሪያው ጎራ የያዛቸውን ተቋሞችን ሁሉ አጠናክሮ መጠነ ሰፊ ዘመቻውን በማፋፋም ሁለተኛውን ጎራ በሰበብ አስባቡ ከፖለቲካው ሜዳ ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ለብቻው በምርጫ በመወዳደር አላማውን ለማስፈጸም እየተጋ ነው። ለዚህም የሀሰት ክስ ፈጥሮ ወደ ግቡ እየገሰገሰ ነው። ይህ ክስ የዝያ እስትራቴጂ አካል ነው። አላማውም ፖለቲካዊ ነው። በመሆኑም የፈጸምኩት ወንጀልም የለም።
ክቡር ፍርድ ቤት፣ በግፈኞች ሴራ የወደቀ የብርቅዬ ልጃችን የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን አስክሬን ለመሸኘትና በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከጓዶቼ ጋር ለመገኘት ያደረኩት ሙከራ እንደ ወንጀል የሚቆጠር ከሆነ ደግሞ ዘላለም ብታሰር አይቆጨኝም። አመሰግናለሁ።
መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም
በቀለ ገርባ
ፊንፊኔ፣ ኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያ