January 7, 2025

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ በሕግ መነጽር ሲታይ!! ባለቤቱ በግልጽ ሳይታወቅ ምርጫ ማድረግ ከህግ አንጻር ፍትሐዊ አይሆንም!!

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ በሕግ መነጽር ሲታይ!! ባለቤቱ በግልጽ ሳይታወቅ ምርጫ ማድረግ ከህግ አንጻር ፍትሐዊ አይሆንም!!


5FD15EB4-2292-4E33-B991-D900AEBC4997

By Andinet Zeleke Bekele


“ፊንፊኔ የአዲስ አበቤዎች ናት” “ፊንፊኔ የሁሉም ክልሎች ህዝብ ናት” “ፊንፊኔ የኦሮሞዎች ናት” ወዘተ የሚሉትን መፈክሮችን ስሰማ፣ ይህ በሌሎች ክልል ዋና ከተሞች የማይከሰት በኦሮሚያ ዋና ከተማ ላይ ብቻ ያተኮረ የባላቤትነት ጥያቄ ምንጩና ዓላማው ምንድነው? የአሶሳና የጋምቤላ፣ የባህር ዳር ወይም የጂጂጋ የሃዋሳ ወይም የሃረር ባለቤትነት ጥያቄ አንድም ቀን ሳይነሳ ለምን የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ያን ያህል ሊገንን ቻለ? ብዬ ራሴን ደጋግሜ ስጠይቅ መልሱን ለማግኘት ወደ ህገ መንግሥቶቹ አቀናሁ።

የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ ህገ መንግሥት፣ አፈጻጸሙ ላይ ችግር ይኖራቸው እንደው እንጂ ቃልና መንፈሳቸው አሉ ከሚባሉ የሌሎች ዲሞክራት አገሮች ህገ መንግሥት ተርታ የሚያሰልፋቸው ስለሆነ ለውዝግቡ መፍትሄ ይሰጣሉ የሚል እምነት አለኝ። ህጎቻችን ግን ፍጹማን ናቸው የሚል ዕብደት አይከጅለኝም። ህገ መንግሥት ግን ከፋም ለማም፣ ዜጎች ተስማምተው የሚበጃቸውን ሌላ ህገ መንግሥት እስከሚያጸድቁ ድረስ፣ ዛሬ ጠቀሜታ ላይ ያሉ ህገ መንግሥቶቻችን ብቸኛ መተዳደርያችን ናቸው።

መሻሻል አለባቸው ተብሎ ከታመነበት ደግሞ የህገ መንግሥቱን ድንጋጌ ተከትለን የተሻለ ህገ መንግሥት የማናጸድቅበት ምክንያት የለም። በዚህ ዕውኔታ ላይ ተመሥርቼ ነው እንግዲህ ይህን ጽሁፌን በሙሉ ለአንባቢያን ምቾት ሲባል ከሁለቱም ህገ መንግሥቶች ለዚህ ሙግታችን ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውንና ለጥያቄዎቻችን ተገቢውን መልስ ይሰጣሉ ብዬ የማምንባቸውን አንዳንድ የክልሉንና የፌዴራሉን ህገ መንግሥት አንቀጾች ለይቼ በማስቀመጥ ሙግቴን ልቀጥልበት።

የፌዴራሉ ህገ መንግሥት፣-

አንቀጽ 46 የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው።

አንቀጽ 47 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሬፑብሊክ አባላት ዘጠኝ ናቸው።

አንቀጽ 49 የፌዴራሉ መንግሥ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት ይሆናል።

አንቀጽ 104 አንድ የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ….. በህዝብ ተወካዮችና የፌዴረሺኑ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛው ድምጽ የደገፈው ከሆነ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ህዝብና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ይቀርባል።

የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሥት፣-

አንቀጽ 5 አፋን ኦሮሞ የክልሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል።

አንቀጽ 6 የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ (ፊንፊኔ) አዲስ አበባ ነው።

አንቀጽ 8 የኦሮሞ ህዝብ የክልሉ መንግሥት የሥልጣን ባለቤት ነው።

አንቀጽ 9 ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ፣ የፖሊቲካ ድርጅት፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባላሥልጣኖቻቸው ይህንን ህገ መንግሥት የማስከበርና ለህገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው።

አንቀጽ 34 በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ”የክልሉን የሥራ ቋንቋ እስካወቁ ድረስ በክልሉ መንግሥታዊ ሥራ ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት፣ እንደማንኛውም የክልሉ ተወላጅ ሰርቶ የመኖር፣ ከስፍራ ስፍራ የመዘዋወር፣ ሃብትና ንብረት የማፍራትና የመያዝ“ መብት አላቸው።

አንቀጽ 39 ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ…..በቀለም፣ በዘር፣ በብሄረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖሊቲካ ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት ……በቀጥታና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካይነት በህዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ …..ዕድሜው አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላ በህጉ መሰረት የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው”

አንቀጽ 44 በክልሉ ውስጥ በሚያካሄዳቸው ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግሥት በቂ ዕርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ የማዘዋወር መብት አለው።

አንቀጽ 98 የዚህ ህገ መንግሥት ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት የቀረበውን የማሻሻያ ሃሳብ የምክር ቤቱ ሶስት አራተኛ አባላት ሲያጸድቁት ነው።

በኔ ግምት፣ የአዲስ አበባን ባላቤትነት አስመልክቶ በአሁኑ ምርቻ እና ከዚህ በፊት በመካሄድ ላይ ስላለው መርዛማ ክርክር መንስኤው የፌዴራሉ ህገ መንግሥት አንቀጽ 49 እና የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሥት አንቀጽ 6 አለመጣጣም ነው። ሁለቱም ህገ መንግሥቶች አዲስ አበባን ዋና ከተማዬ ነው ብለው አስቀምጠዋልና! በህገ መንግሥቱ መሰረት ኢትዮጵያ የተዋቀረችዉ ሲዳማን ጨምሮ በአስር ክልሎች ነው። በሌላ አነጋገር፣ የኢትዮጵያን ምድር የተከፋፈሏት እነዚህ አስር ክልሎች ሲሆኑ ከነዚህ አስር ክልሎች ተርፎ ለሌላ ዓላማ የተቀመጠ አንዲት ካሬ ሜትር የኢትዮጵያ ምድር የለም። በመሆኑም፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ አስሩ ክልሎች ከተከፋፈሉት “ይዞታ” ውጪ ነጻና የራሱ የሆነ ልዩ ክልል ወይም ተከልሎ የተሰጠው ቁራጭ መሬት የለውም። ስለዚህ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ፣ መንግሥታዊ መዋቅርና ቢሮክራሲያዊ አስተዳደር ስናወሳ ስለነዚህ አስር ክልሎችና በነዚህ ክልሎች ውስጥ ስለሚኖሩ ህዝቦች እንጂ በፌዴራሉ “ክልል” ስለሚኖር ህዝብ አለመሆኑ ግልጽ ነው።

አንድ የፌዴራሉ አባል የሆነ የክልል ዋና ከተማ እንዴት የፌዴራሉም ዋና ከተማ እንደሆነ ባይገባኝም አንድ ከተማ የፌዴራሉም የክልሉም ዋና ከተማ ሊሆን እንደሚችል አውቃለሁ። ስለዚህ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የፌዴራሉ መንግሥት ከተስማሙ አዲስ አበባ የሁለቱም ዋና ከተማ የማትሆንበት ምክንያት አይታየኝም። በተቃራኒው ግን፣ አዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መሥርያ ቤት ያለበትና የዲፕሎማቲኩ ማህበረሰብ መናኸርያ ስለሆነች የፌዴራሉ መቀመጫ ብቻ መሆን አለባት የሚለውን መሰረተ ቢስ ክስ መቀበል ያዳግታል።

በተለምዶ አዲስ አበባ የፊውዳሊስት ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስለነበረች ዛሬም ያ አሓዳዊ ሥርዓት ተገርስሶ አገሪቷ በፌዴራሊዝም ሥርዓት መተዳደር ስትጀምርና ኢትዮጵያ በዘጠኝ (በአሁኑ ወቅት አስር) ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩ ክልሎች ስትከፋፈል፣ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነገር አድርገው የሚያዩ ወገኖች አሉ። ቢሆን ጥሩ ነበር፣ ዕውኔታው ግን ከዚህ ለየት ያለ ነው። በ 1995 ዓ/ም ህገ መንግሥቱ ሲረቅቅ ስለነበረው ውይይት የቃለ ጉባኤውን ቅጂ ማግኘት አልቻልንም እንጂ፣ ኢትዮጵያ በዘጠኝ ክልሎች እንዴት እንደ ተከፋፈለች፣ ለምን ለፌዴራሉ መቀመጫ የሚሆን ስንዝር መሬት እንኳ እንዳላስቀሩ፣ ከዚያም ደግሞ በምን ምክንያት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ የፌዴራሉም ዋና ከተማ እንደሆነች ለማወቅ ይቻል ነበር።

በሁለቱ ተቋማት መካከል ማለትም በኦሮሚያና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል የተካሄደ አንዳች ዓይነት የምሥጢር ስምምነት ይኖራል ብዬ እገምታለሁ። አንዳች ዓይነት የሁለትዮሽ ውል ባይኖር ኖሮ ኩርማን መሬት እንኳ የተነፈገውና ግንድ የሌለው የፌዴራሉ መንግሥት “አዲስ አበባ ዋና ከተማዬ ናት፣ በመሆኑም እኔ ነኝ የማዝበት” ከማለት ባሻገር ለክልሉ ባለቤት “ልዩ ጥቅም” ጠባቂና አስጠባቂ አይሆንም ነበር። በራሱ ስም የተመዘገበ ስንዝር የምታክል መሬት የሌለው ሰው በራሱ ስም የቤት ካርታ ሲኖረው እንደ ማለት ነው።

በፌዴራሉ ህገ መንግሥት በተደተደነገገው መሰረት ዘጠኙ የፌዴራሉ አካላት የየራሳቸው የሆነ የክልላቸው ርዕሰ ከተማ አላቸው። ባቋቋሙት ክልላዊ ፓርላማና፣ ፓርላማዎቹም ባጸደቋቸው ህጎች ተመርተው ያለፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት፣ በርዕሰ ከተሞቻቸው ጭምር፣ ክልላዊ የአስተዳደር መዋቅር ዘርግተው ራሳቸውን ያስተዳድራሉ። የፌዴራሊዝም ዋና መገለጫውም ይኸው ነውና። የአማራው ክልል በባህር ዳር፣ የደቡብ ህዝቦች በሃዋሳ፣ ጉሙዝና ቤኒሻንጉል በአሶሳ እና የትግራይ ክልል ደግሞ በመቀሌ ከተሞች ላይ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም የሚረዳ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግተው የክልላቸውን ነዋሪ ህዝብ መብትና ጥቅም እያስጠበቁ ይገኛሉ።

በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም የክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ የራሱን አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግቶ የክልሉ ነዋሪዎችን መብትና ጥቅም እያስጠበቀ ነው። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ያልኩት፣ የክልሉን ዋና ከተማ አዲስ አበባን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ በሌሎች የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ያለውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ባግባቡ የተጠቀመበት ስለማይመስለኝ ነው። ለምሳሌ የክልሉ የመሥርያ ቋንቋ የሆነው ኦሮሚኛ ቋንቋ በአዲስ አበባ የመሥርያ ቋንቋ አልሆነም። በሌሎቹ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች እንደሚያደርገውም፣ በክልሉ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ የራሱን አስተዳደራዊ መዋቅርም በሥነ ሥርዓት አልዘረጋም። ለምን?

ዛሬ በወረቀት ደረጃ ያለው ”የቃላት“ ጥይት የመወራወሩ ጉዳይ ነገ ወደ እውነተኛ ጥይት ወይም ዱላ ሊቀየር ይችላል የሚል ሥጋት አለኝ። ችግሩ ደግሞ በጊዜ ካልተፈታ የባሰ አደጋ ሊያመጣ ይችላል። ታዲያ ምን መደረግ አለበት? ለማንኛውም ሰው ሰራሽ ችግር ሰው ሰራሽ መፍትሄ አለው ይላል ኦሮሞ ሲተርት። እኔም በዚህ እስማማለሁ። ችግሮቹ የተፈጠሩት በሰዎች ስለሆነ መፍትሄውም በሰዎች እጅ ላይ ነው። የእያንዳንዱ ህብረተሰብ ችግር ደግሞ የየራሱ የሆነ ይዘትና አፈጣጠር ስላለው የሌሎች አገር ተሞክሮዎችን እንዳለ ተውሶ ላገራችን ይሆናል ብሎ ማሰብ ትክክል አይመስለኝም። ለሁሉም ግጭቶች መፍቻ የሆነ አንድ ወጥ ሳይንሳዊ ፎርሙላ ስለሌለ ከዚህ በታች የማቀርበውንም መፍትሄ ከዚያ አንጻር እዩት ለማለት ያህል ነው። ከዚያ በፊት ግን በህገ መንግሥቱ መሰረት ሥራ ላይ መዋል ያለባቸውና በንትርክና ወከባ ሊቀየሩ የማይችሉ ዕውኔታዎችን ላስቀምጥና ወደ መፍትሄዎቹ ልዝለቅ።

ባጠቃላይ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ” ባገራችን ሲነሱ ከነበሩና እየተነሱ ካሉ የፖሊቲካ ጥያቄዎች በጣም ለየት ያለ ነው። በመጀመርያ ደረጃ፣ የኢትዮጵያን መሬት በግል ሃብትነት መያዝ እንደማይቻል እየታወቀ አዲስ አበባን “የኔ ነው” “የኛ ነው” “የአዲስ አበቤዎች” “ወይም “የሁሉም ብሄር ተወላጆች” ነው ብሎ መሞገት ጉንጭ አልፋ ክርክር ይመስለኛል። አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ መሆኗ እየታወቀና የኦሮሞሕዝብና ሌሎች የክልሉ ህጋዊ ኗሪዎች ደግሞ የክልሉ የሥልጣን ባለቤት መሆኑ በህገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ ተነድፎ እያለ፣ አዲስ አበባ ከአስሩ የፌዴራሉ ክልል አባላት በአንዳቸውም ያልተጠቃለለች እንደው በአየር ላይ የተንጠለጠለችና ከክልሎች አስተዳደራዊ መዋቅር ውጪ እንዳለች አስመስሎ ማቅረብና የተለየ ባለቤትነትን መጠየቅ ህገ መንግሥቱን መገዳደር ነው።

አዎ፣ ህገ መንግሥቱ የህዝቡን ጥቅም አያስጠብቅም ተብሎ ከታመነበት ህጉን ተከትሎ የማይቀየርበት ምክንያት የለም። ይህ ደግሞ ህጋዊ ነው። ከሚቀጥለው የፓርላማ ምርጫ በኋላ ለሚሰየመው የህዝብ ተወካዮች ጉባኤ ላይ አቅርቦና አወያይቶ ህጋዊ በሆነ መንገድ ማስቀየር ብቻ ነው። እስከዚያ ድረስ ግን ወደድነውም ጠላነው፣ በህገ መንግሥቱ መሰረት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ናት። የክልሉ የሥልጣን ባለቤት ደግሞ የኦሮሞ ህዝብና በህጋዊነት በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ነው፣ አራት ነጥብ::

About Post Author