“የዋልታ ዘገባ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ሴራ ነው” የትግራይ ክልል
“የዋልታ ዘገባ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ሴራ ነው” የትግራይ ክልል
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ያስተላለፈውን ”የውሸት ዜና በቸልታ” አልመለከተውም አለ።
ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዛሬ አመሻሽ ላይ በፌስቡክ ገፁ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት ደህንነትን በማስመልከት ያወጣው ዜና ስህተት መሆኑን ጠቅሶ ወዲያው ይቀርታ ቢጠይቅም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ግን ጉዳዩን በቀላሉ እንደማያልፈው ገልጿል።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሊያ ካሳ፤ ዋልታ ኢንፎረሜሽን ማዕከል ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ የሐሰት ነው ያሉ ሲሆን ጉዳዩን ወደ ሕግ እንደሚወስዱትም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ይህ ዘገባ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ሴራ ነው ብለን ነው የምንረዳው። በይቅርታ የሚታለፍም አይደለም” ያሉት የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊያ፤ የዚህ አይነት ዘገባ ወዳልተፈለገ ሁከት ሊያስገባ ይችላል ብለዋል።
ዶ/ር ደብረጽዮንም በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው በእርሳቸው ደህንነት ላይ የተሰራው ዘገባ የሃሰት መሆኑን ገልጸዋል።
በትግረኛ ባሰፈሩት አጠር ያለ ጽሑፍ “በህዝብ እና በፓርቲው ላይ ሲካሄድ የቆየው የስም ማጥፋት አካል ነው” ብለውታል።
ዋልታ ከሰዓታት በፊት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝደንት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ”ባልታወቀ አደጋ ህወታቸው ማለፉን መቀሌ ከሚገኘው ሪፖርተራችን ሰምተናል” ብሎ ዘግቦ ነበር።
ዋልታ ይህን ዜና ከገጹ ላይ ካነሳው በኋላ፤ ”ዜናው ከተቋሙ እውቅና ውጪ” የተላለፈ እንደሆነና ጉዳዩ እንዴት እንደተፈፀመ አጣርቶ እንደሚያሳውቅ ጠቅሶ ይቅርታ ጠይቋል።
ወ/ሮ ሊያ ካሳ “ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ወደ ዋልታ ደጋግመን ብንደውልም ስልክ ስለማያነሱ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲም በጉዳዩ ላይ የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።