January 4, 2025

የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛናዊነት ማስተካከል ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው – ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ

በዚህ አመት የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛናዊነት ማስተካከል ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ያለፈውን አንድ ዓመት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የለውጥ ሂደት የሚቃኘው አዲስ ወግ መድረክ መዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

PM Abiy

በዚህ አመት የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛናዊነት ማስተካከል ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ያለፈውን አንድ ዓመት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የለውጥ ሂደት የሚቃኘው አዲስ ወግ መድረክ መዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛናዊነት ማስተካከል የበጀት አመቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስት ወጪን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ። በቀጣይ ሃገሪቱ የምትከተለውን የኢኮኖሚ እሳቤ የተመለከተ ዝርዝር ጥናት መዘጋጀቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ ሀገሪቱ ከፍተኛ የእዳ ጫና ስላለባት ተጨማሪ ብድር እንዳትውስድ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከኢኮኖሚው ጋር ተያይዞ የመስኖ ልማትና ቱሪዝምን ማስፋፋት የትኩረት ማዕከል መሆኑን አንስተዋል። ከወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ባደረጉት ንግግርም አሁን ላይ የሰከነ ውይይት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።በፖለቲካው የሚስተዋለው በሽታና ችግር በልሂቃን፣ በአክቲቪስቶች እና በፖለተከኞች ላይ መሆኑንም በንግግራቸው አውስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ልግመኝነት፣ ህሊና ቢስነት እና አቅላይነት እንዲሁም ከሌላ አካል ወደ እኛ የሚገቡ አስተሳሰቦች ለፖለቲካው መበላሸት ምክንያት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። ፖለቲከኞችም ጊዜን በማሻገርና ትናንት ከዛሬ ጋር በማዛመድ ትውልድ መቅረጽ ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያውያን የበዛ ጥላቻ፣ በቀል እና አለመግባባት አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ብዙ ችግር ተሸክሞ መጓዝ ስለማይቻል ይህን ማራገፍ መቅረፍ ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። በሃገሪቱ የፖለቲካ ዋልታ ረገጥነት እንደሚስተዋል ጠቅሰውም፥ ኢትዮጵያ እንድትቆይና እንዳትፈርስ የሚፈልግ ዜጋም ከአፍራሽ ሃሳቦች መራቅና በእነዚህ ሃሳቦች ከመዳከር መራቅ እንዳለበትም ገልጸዋል። በሃገሪቱ የሚስተዋለው ሁኔታ የመስከን ጊዜ ላይ እስከሚደርስም የሚታየው ፅንፈኝነትና ዋልታ ረገጥነት ለጥቂት ጊዜ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።

በሃገሪቱ በማህበራዊ የትስስር ገጽ በተለይም በፌስ ቡክ አጠቃቀም ዙሪያ ችግር እንዳለ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህን ለማስተካከል የሚያግዝ ህግ እየተዘጋጀና ከፌስ ቡክ ኩባንያ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ንግግር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። አዲስ አበባን በተመለከተ የባለ አደራ መንግስት በሚል የሚስተዋለው አካሄድም አግባብና ህጋዊ ያልሆነ መሆኑንም ነው የገለጹት። የውጭ ግንኙነትን በሚመለከት ባለፈው አንድ አመት ብዙ አመርቂ ስራ መሰራቱን አስታውሰው፥ ከኤርትራ ጋር የ20 አመታት የጦርነት እና ፍጥጫ ማርገብ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በተሰራ የዲፕሎማሲ ስራ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ኢትዮጵያን በመስማት ዜጎቿን ማክበር እንዲችሉ ያስቻለ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል። ከቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ምርጫው በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲካሄድ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ በምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲ ቢያሸንፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስልጣን እናስረክባለን ብለዋል።

በሌላ በኩል ቻይና ለአዲስ አበባ የወንዞች ልማት ፕሮጀክት ወጪ ከሚደረገው ገንዘብ ውስጥ ¼ የሚሽፍን ብድር ለመስጠት ቃል ገብታለች። የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትም መጠኑ ያልተገለጸ የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን፥ ኢትዮጵያውያንም የራሳቸውን ኢንቨስትመንት የሚያዋጡ ይሆናል።

About Post Author