የቆጠራ ካርታ ባልተዘጋጀላቸው አካባቢዎች የህዝብ እና ቤት ቆጠራው በልዩ ሁኔታ ይካሄዳል
ካርታው ከተዘጋጀ በኋላም የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶባቸው ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ባለፉት ሁለት አመታት ጥረት ተደርጎ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጥቂት አካባቢዎች መኖራቸውን በኤጀንሲው የካርቶግራፊ እና ጂ አይ ኤስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጉታ ይናገራሉ።
የቆጠራ ካርታ ባልተዘጋጀላቸው የተወሰኑ አካባቢዎች የህዝብ እና ቤት ቆጠራው በልዩ ሁኔታ እንደሚካሄድ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ባለፈው አመት መካሄድ የነበረበት 4ኛው ብሄራዊ የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መጋቢት 29 ቀን ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ነው። ለቆጠራው የሚያስፈልጉ የግብዓት ስርጭት እና የቆጠራ ተቆጣጣሪዎች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ስልጠናም እየተካሄደ ይገኛል።
ይሁን እንጅ ከቆጠራው አስቀድሞ የቆጠራ ካርታ ያልተሰራላቸው ቦታዎች እንዴት ሊቆጠሩ ነው በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ ከቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌና ሃረሪ ከተውጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምላሻቸው የህዝብና ቤት ቆጠራው ዋነኛ አላማ ትክክለኛ የኢትዮጵያን ህዝብ ቁጥር ማወቅ መሆኑን ጠቅሰው፥ ብዙ ቁጥር ለመያዝ የሚደረግ ሽሚያ ካለ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል። የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በበኩሉ በክልሎች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች መካከል የቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸውን ይገልጻል።
ለቆጠራው በመላ ሀገሪቱ ከ152 ሺህ በላይ ካርታ ሲዘጋጅም በእነዚህ አካባቢዎች ጥንቃቄ ተደርጓል ነው ያለው። ካርታው ከተዘጋጀ በኋላም የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶባቸው ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ባለፉት ሁለት አመታት ጥረት ተደርጎ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጥቂት አካባቢዎች መኖራቸውን በኤጀንሲው የካርቶግራፊ እና ጂ አይ ኤስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጉታ ይናገራሉ። ከኤርትራ ጋር ቀደም ብሎ በነበረው ችግር ሳቢያም 16 የአፋር ክልል ቀበሌዎች እንዲሁም ሞያሌ ከተማ የቆጠራ ካርታ አለመዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።
የቆጠራ ካርታዎቹ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍና በእግር በመንቀሳቀስ የተዘጋጁ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም ቆጠራው በሚካሄድባቸው ታብሌቶች ላይ እየተጫኑ ይገኛሉ። ካርታ ያልተዘጋጀላቸው አካባቢዎች ላይም ኤጀንሲው በሚከተለው ልዩ የቆጠራ ዘዴ መሰረት ቆጠራው ይካሄዳል ነው ያሉት።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙም በ4ኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ የማይቆጠር ሰው እና ቤት አለመኖሩን ጠቅሰው፥ የቆጠራ ካርታ ባልተዘጋጀላቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች እና ቤቶች በልዩ ሁኔታ ይቆጠራሉ ብለዋል።
የአፋር ክልል 16 ቀበሌዎች የቆጠራ ካርታ ባይዘጋጅላቸውም ከሌላ ወገን የሚነሳ ቅሬታ ስለሌለባቸው ቆጠራው ሲሰራ ለአፋር የሚደመር ይሆናል። የሞያሌው ግን በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች መካከል ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ ቆጠራው ሲከናወን ለሁለቱም ክልሎች ሳይደመር ቁጥሩ በብሄራዊ ደረጃ እንደ ግብዓት ይውላል ተብሏል።
ኤጀንሲው የይገባኛል ጥያቄዎችን የመመለስ ስልጣን እንደሌለውና ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ጭምር ቆጠራው እንደሚካሄድ ጠቅሶ፥ ጥያቄው ምላሽ ሲያገኝ የቆጠራው ውጤት ወደተወሰነለት አካል ይደመራል ብሏል። 4ኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ያለምንም ሳንካ እንዲካሄድም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራውና የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በበላይነት እያስተባበረ ይገኛል።