November 27, 2024

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል የገባውን ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አጠፈ

የዓለም ባንክ የኮሮና ቫይረስ ጫናን ለመከላከልና ለሰብዓዊ ስራዎች ከሚውሉ ጉዳዮች ውጭ ለኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብር ሊያቀርበው የነበረውን ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ደጋፍ (ብድርና ድጎማ) እንደማያቀርብና ከኢትዮጵያ ጋር በዚህ ረገድ የገባውን ስምምነት እንዳቋረጠ ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ ሰምታለች።

img_3671

September 2, 2020

ባንኩ ኢትዮጵያ ቃል በገባችው መሰረት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እየተገበረች አለመሆኑን በምክንያትነት አንስቷል።

ዋዜማ ራዲዮ- የዓለም ባንክ የኮሮና ቫይረስ ጫናን ለመከላከልና ለሰብዓዊ ስራዎች ከሚውሉ ጉዳዮች ውጭ ለኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብር ሊያቀርበው የነበረውን ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ደጋፍ (ብድርና ድጎማ) እንደማያቀርብና ከኢትዮጵያ ጋር በዚህ ረገድ የገባውን ስምምነት እንዳቋረጠ ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ ሰምታለች። የአለም ባንክ እርምጃውን የወሰደው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብሮችን ቃል በገባችው መሰረት በሙሉ ይዘቱ አልተገበረችም በሚል ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ አመት ወይም 2012 አ.ም ሲጀመር አንስቶ ለሶስት አመታት ተግባራዊ የምታደርገውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ይፋ ስታደርግ ያስፈልገኛል ካለችው አስር ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ውስጥ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር የወጪውን ስልሳ በመቶ እንደሚሸፍን ቃል የገባው የዓለም ባንክ ነው። የዓለም ባንክ እስከ ሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስን ገንዘብ በብድር ለማቅረብ ተስማምቶ ነበር።

በሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብሩም ኢትዮጵያ የምንዛሬ ተመኗ በገበያ እንዲመራ ፣ የመንግስት ንግድ ድርጅቶችን ወደ ግል ማስተላለፍ (የፕራይቬታይዜሽን) ሂደቱን እንዲፋጠን ፣ የመንግስት ገቢና ወጭ እንዲመጣጠን ፣ የግሉን ዘርፍ ማበረታታትና መሰል ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንድታደርግ ይጠበቅ ነበር። ሆኖም በአለም ባንክ እና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት በኩል የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራዎች ፈጣን አይደሉም የሚሉ ቅሬታዎች ቅሬታዎች ሲቀርቡ ስንብተዋል።

 በአንዳንድ የኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያዎች ዙርያም ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ; አይኤምኤም ; እና ዓለም ባንክ ሲሰሩ ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ተቋማት አማካሪ ተብለው የመጡ ባለሙያዎችና እና ነባር የሀገር ቤት ባለሙያዎችና ሀላፊዎች መሀል ብዙም የሀሳብ መቀራረብ እንደሌለ ሰምተናል።
ቀድሞም በሀገር ውስጥ በኢኮኖሚ ተቋማት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ እና አሁንም በኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች የማሻሻያ ትግበራዎቹ መፋጠናቸው ከባድ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ከአለማቀፍ ተቋማት የመጡት ባለሙያዎች ደግሞ ይተግበሩ የሚባሉት የማሻሻያ ስራዎች መፍጠናቸው የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ጫና በመረዳት ይሁን ባለመረዳት ሂደቱ እንዲፋጠን ሰፊ ጫና እያካሄዱ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ ኢትዮጵያ በገበያ የሚወሰን የምንዛሬ ተመን የሚኖራት ከሶስት አመት በሁዋላ ነው ይበሉ እንጂ : ይህ ጉዳይ አለም አቀፍ አበዳሪዎችን ያስደሰተ አይመስልም። እነ ዓለም ባንክ ና አይ ኤም ኤፍም ሀገሪቱ ብሯን አሁን ካለው ፍጥነት በጨመረ መልኩ እንድታዳክም እና በቶሎ በገበያ ወደ ሚወሰን የምንዛሬ ተመን አሰራር እንድትገባ ጫና እያደረጉ እንዳለ ዋዜማ ራዲዮ መረጃ አላት።

አለማቀፍ ተቋማቱ ብርን ከዚህ በበለጠ ፍጥነት አዳክሞ የውጭ ምንዛሬ ተመን በፍጥነት በገበያ ወደሚወሰንበት አሰራር እንዲገባ ይፈልጋሉ።ሆኖም የብሄራዊ ባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ በገበያ የሚወሰን የምንዛሬ ተመን የሚኖረው ከሶስት አመት በሁዋላ ነው ማለታቸው ከአበዳሪዎች ፍላጎት ጋር ብዙ የተጣጣመ አይመስልም።

ከህዳር ወር ጀምሮ እስከ አሁን የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ በእየ እለቱ በፍጥነት መዳከሙ ከዋጋ ግሽበት ባለፈ ብዙም ያመጣው ለውጥ የለም።ምርታማነት ባላደገበትና ኢትዮጵያ በአመዛኙ ምርት አስገቢ በሆነችበት ሁኔታ ወደ ገበያ መር የምንዛሬ ስርአት መገባቱም የኢኮኖሚ ጫናውን ይበልጥ ያበረታዋል። ይህና ሌሎች ይተገበራሉ የተባሉ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች አልፈጠኑም በሚል ነው የዓለም ባንክ የገባውን ውል አቋርጫለሁ ያለው።

ይሁንና ኢትዮጵያ ዘግየት ብላም ቢሆን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም አሜሪካንን ስላላስደሰታት በአለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት በኩል እያደረገቸው ያለው ጫና ጋር እንደሚያያዝ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዋዜማ ራዲዮ ምንጭ ገልጸዋል።አሜሪካ በራሷ በቀጥታ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታ ብዙም ስላልሆነ ብዙ ጊዜ ተጽእኖን ማሳረፍ የምትፈልገው በምትዘውራቸው ተቋማት በኩል ነው ይላሉ እኚሁ የዋዜማ ራዲዮ ምንጭ።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ሱዳን ሲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ካርቱም ያቀኑት በዚሁ የህዳሴው ግድብ ድርድር እና የዓለም ባንክ ጉዳይ ላይ አግኝተው ሊያወሯቸው ፈልገው እንደሆነ መረዳት ችለናል።በቅርቡ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ የነበረው 130 ሚሊየን ዶላርን እንዲዘገይ የወሰነችው ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም እንድትቀይርና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በፍጥነት እንድትተገብር እጅ ለመጠምዘዝ ታስቦ እንደሆነም ታውቋል። [ዋዜማ ራዲዮ]

About Post Author