November 24, 2024

ያላመንኩበትን አላደርግም፤ ያመንኩበትን ከማድረግ አልቆጠብም።

(By Ezekiel Gebissa)

ሕገ-መንግስትንና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን ማዳን በሚል መሪ ቃል በመቐለ የተካሄደው ጉባኤ ላይ ሕዝቅኤል ገቢሳ ተሳተፈ በሚል ርዕስ የFacebook ክስተት ሆኖ ውሏል። ይህን ዘመን ከሳሾቼ በዋናነት “የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች” እና የኦዴፓ (አሁንም ሕግ የሚያውቀውድርጅት) ተቀጣሪ ተላላኪዎች ናቸው።ለነዚህ መልስ መስጠት ከነርሱ ጋር መጨቅየት ነው ። አጭሩ መልስ፣ “አያገባችሁም!” ነው። እነዚህን በጨለማ እንጂ በብርሃን ወጥተው አቋማቸውን መግለጽ የተሳናቸውን ድኩማን ተቀጣሪዎች፣ ጥርቅም አድርጎ መዝጋት ነው ተገቢው መልስ።

ቀጥሉ። እናንተ በጮሃችሁ ቁጥር፣ ቁርጠኝነታችን ይጠነክራል።

ነገር ግን እናንት የምታነሱት አቧራ አይኑ ውስጥ ገብቶ ብዥ የሚልበት ንፁህ ህዝብ አለ። ለነሱ ስትል ማብራሪያ ብትሰጥ ይሻላል የሚሉኝ ወዳጆቼ ደስ ይበላቸው። የኔ መልስ ይሄው፦

“በስፍራው የተነገረው ነገር እውነት ቢሆንም መቐለ ላይ ሊነገር አይገባም” የሚሉ ተመፃዳቂዎች አሉ። እውነት በመልክአ ምድር አይወሰንም። እኔ የማውቀዉን እውነት ቦታና ሁኔታ አይቼ ሳይሆን የምናገረው እውነት ስለሆነ ነው። የተመቻቸ ቦታና ጊዜ መፈለግ አድርባይነት ነው። የነፍጠኞችና የትምክህተኞች ሸፍጥ ነው። የኦሮሞን ህዝብ ሀቅ በየትም ቦታ፣ በማንም ፊት፣ በየትኛውም ሰዓት እናገራለሁ። ወደፊትም ትንፋሽ እስካለኝ ድረስ እቀጥላለሁ ።

ህወሓት ባዘጋጀው መድረክ መካፈል ህወሓትን መደገፍ ይሆናል የሚሉ ይሉኝታቢስ አይን አውጣዎችም አሉ ። አሁን በሥራ ያለው ህገ መንግሥት (አንቀፅ 8 (1፣2፣3 እንዲሁም አንቀፅ 39ንያጠቃለለው) እና ሕብረብሔራዊ የፌደራል ሥርዓት የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ ያገኘው ድል ነው እንጂ የህወሓት ስጦታ አይደለም። ነፍጠኞች አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት እና ህብረብሔራዊ የፌደራል ስርአትንይቅርና ብሄሮችንና ብሔረተኝንትን የፈጠረው ህወሓት ነው ይሉናል። ተባባሪዎቻቸው ደግሞ የነፍጠኛ ስርአት አቀንቃኝ የሆኑ የኦዴፓ ተቀጣሪዎች ናቸው። ሌሎቻችሁ ከነዚህ ጋር ሆናችሁ ሳታውቁ የነፍጠኞችና የትምክህተኞችን ክስ አታራምዱ። “ሕገ መንግስቱ እና ህብረብሔራዊ የፌደራል ስርአት መጠበቅ አለበት” ብሎ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መናገር ህወሓትን መደገፍ ነው ብሎ ክስ ማቅረብ፣ የደንቆሮ ክርክር መድገም ነው ።

ለወደፊቱም አንድ ነገር ግልፅ ይሁን። እኔ ባሁን ሰዓት ከህወሓት ጋር የተለየ ትግል የለኝም። ከህወሓት ጋር እጅግ መራር ትግል ተደርጎ ስድስት ሺህ ነፍስ ገብረን፣ ብዙዎች ተሰደው፣ መቶ ሺህዎች ታስረው ተሰቃይተው በድል አድራጊነት ወጥትናል። አልሰማችሁ እንደሆነ እንጂ ህወሓት ዘርግቶት የነበረው የአምባገነን ስርአት ተሸንፎአል። ያሸነፍነውን ትግል ደግመን አንገጥምም። ህወሓት ትናንት ሕገ መንግስቱና ህብረብሔራዊ የፌደራል ስርአቱን ተጠቅሞ ከፍተኛ በደል አድርሶአል። ለዚያም በደል ኢህአዴግ ይቅርታ ለምኖ ነው ያለንበት ለውጥ “ትልቅ ተሃድሶ” አድርገዋል ለተባሉ የኢህአዴግ አባላት በአደራ የተሰጠው።

የነበረው አምባገነንነት ህወሓት መራሽ ነበር ቢባልም፣ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ነበር። አብረዉ ነው የበደሉት፣ አብረው ነው ጥፋታቸውን ያመኑት፣ አብረው ነው የኢትዮጵያንን ህዝብ ይቅርታ የለመኑት። የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ አድርጎ ከሆነ፣ ይቅርታው ለኦዴፓ፣ ለአዴፓ እና ለደኢሕዴን ተስጥቶ ህወሓት ዘንድ ሲደርስ ይቆማል የሚል አስተሳሰብ፣ ከኔ የሞራል መርህ ጋር አይጣጣምም።

ከኦዴፓ እየተመፀወቱ የሚኖሩ ብልሹዎች እኔን ለመተቸት የሞራል ልዕልና የላቸዉም። አስተሳሰቡ ሎጂክም የለዉም። በኦዴፓ መሪዎች ስሌት ለ27 ዓመት የህወሓት ተላላኪ የነበሩት እራሳቸው ነበሩ። በነሱ እሳቤ ከሄድን ህወሓት አዛዥ ነበር፣ ኦዴፓ የወንጀሉ ፈፃሚ ነበር። ሁለቱም እኩል ወንጀለኞች ናቸው። የተግባር ወንጀለኛ የነበረው ገዳዩ አሳሪው አሳዳጁ አባራሪው የመሬት ቸብቻቢው ኦዴፓ ነበር። ኦዴፓ “የለውጥ መሪ”፣ ህወሓት ግን ብቸኛ ተጠያቂ የምትለዋ ዘይቤ ቀሽም የሌባ ታክቲክ ነች። አሁን በመፈንቅለ መንግሥትና ዘርን በማጥፋት ወንጀል ሊከሰስ የሚችል አዴፓ ጋር እየሰሩ ትናንት በሰራው ወንጀል ተጠያቂ ነው ከሚባል ህወሓት ጋር አንነካካም ማለት አይቻልም። ከዐብይ አህመድ ወይም ደመቀ መኮንን ጋር ሸራተን ሲሳሳሙ መዋል ፅድቅ፣ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የተገኝበት ስብሰባ ለይ (በskype) መገኘት ግን ኃጢያት ነው የምትል አካሄድ፣ አታዋጣም።

ህወሓትን መጥላት መብት ነው። በህወሃት ምክንያት ግን ትግራይን የኢትዮጵያ አካል እንዳልሆነ መቁጠር መቆም አለበት። ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በትግራይ ላይ ከፍተኛ በደል በመፈፀም ላይ ያለው የህወሓት የወንጀል ተላላኪ የሆነው የኦዴፓ(እና የአዴፓ) አመራር ነው።

“ትናንት የኦሮሞን ህዝብ ሲጨፈጭፍ ከነበረዉ ህወሓት ጋር መታየት ትክክል አይደለም” የሚል መመፃደቂያም አይሰራም። ትናንትስ ትናንት ነው። ዛሬስ? በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ የኦሮሞ ተማሪዎችን እየገደለ የተረፉትን አስሮ እያሰቃየ ያለው ከአዴፓ ጋር የሚሰራውና ካልተረጋጋችሁ ዩኒቨርሲቲውን እዘጋለሁ እያለ በወጣቶች ስቃይ የሚያላግጠው አብይ አህመድስ? ከግድያ አደጋ ሸሽተው ፍንፍኔ ደርሰው አቤት ሲሉ “እኔን አይመለከተኝም” ብሎ የበተናቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መሪ ተብሎ ቢሮ የተሰጠው ግለሰብስ? የወለጋንና የጉጂን፣ የቦረናን ህዝብ ላንድ ዓመት ተኩል በኮማንድ ፖስት ጠፍሮ እያሰቃየ ያለው፣ በጊዳሚና በቤጊ አካባቢ በሄሊኮፕተር ጋንሺፕ የደበደበው አመራርስ ? መግቢያ መውጫ አሳጥቶ ወጣቶችን በጥይት ሲደፋ የሚውለውስ? በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኦሮሞዎችን እስር ቤቶች ስላልበቁት ቤተመንግሥትና የቀበሌ ቤቶችን እንዲሁም የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፖችን የኦሮሞዎች ማጎሪያ ያደረገውስ? የራሱን ወንጀልና አገር የማስተዳደር ድክመቱን ሁሉ በህወሓት ላይ እያላከከ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረግ ታክቲክ እምብዛም እርባና የለውም።

ለማንኛዉም “ኦዴፓ ኦሮሞ ነው። ባይሆን እቤታችን ውስጥ እንመካከር እንጂ ገመናችንን በአደባባይ አንናገር፣ እዚሁ በጓዳችን እናሾክሹክ” የምትሉ ወዳጆች” እንዲህ ያለ አባባል እየተካሄደ ያለዉን ወንጀል የፖለቲካ አሻጥርና አገር የሚያጠፋ ወንጀል እንሸፋፍን ማለት ስለሆነ ወዳጅነቱ ይቅርብኝ እንጂ ከናንተ ጋር ተባባሪ አይደለሁም።

በትግራይ ክልል መገኘት ራሱ ከህወሓት ጋር ትብብር ነው ለምትሉ ነሆላሎች፣ እኔ ጊዜ ስላልፈቀደልኝ ነው እንጂ ገና ብዙ ለመጎብኘት የምፈልገው የትግራይ ክልል ከተሞች አሉ። የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ተወካዮች በትግራይ ስለተሰበስቡ ለነሱ መናገር ጥፋት ነው የምትሉ የአዕምሮ ድንኮች ናችሁ። የራሳቸውን ህዝብ ወክለው በግልፅ ቋንቋና ወደር በሌለው ጀግንነት የህዝባቸውን እውነት የተናገሩት ታላላቅ ሰዎች የተገኙት ከዚያው ከመቐለ ስብሰባ መድረክ ነበር ።

ማንም ሰው እስካሁን በዚያ መድረክ የተናገርከው የኦሮሞን ህዝብ ትግል ይጎዳል ወይም እውነት አይደለም አላለኝም። ዋናዉ ክስ ህወሓት ላይ ቂም ይዘህ መቆየት አለብህ ነው። እሱ፣ ፖለቲካ አይደለም። እኔ፣ የኦሮሞን ህዝብ እውነት ለኔ በገባኝ መጠን ከመናገር አልቦዝንም–በመቐለ ይሁን በሶማሌ። ይህን በማድረጌ፣ ህወሓት 2 ሚልዮን ብር የሚሰጠኝ ከሆነ፣ ወሮታቸውን ከፍዬ አልጨርስም። ለማንኛዉም እስካሁንም ድረስ ተከፍሎኝ የሰራሁት ለቀጠረኝ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነው። ልሳኔን ለፖለቲካ አከራይቼ አላውቅም። የኦዴፓ የክፍያ መዝገብ ላይ ያሉ ምንደኛ ታጋዮችን እዚያው የነሱ መንደር ዉስጥ ፈልጉአቸው።

Ezekiel Gebissa.

About Post Author